Skip to main content
tmdnews3

በክልሉ ሚፈፀም ህገ-ወጥ የንግድ እንቅስቃሴ ለመከላከልና ለመቆጣጠር የወጣው መመሪያ ቁጥር 01/2017 ላይ ከተቀመጡ አስተዳደራዊ እርምጃዎች መካከል በጥቂቱ:- መጋቢት 03/2017 ዓ/ም

መጋቢት 03/2017 ዓ/ም

• ማንኛውም ሰው የንግድ ፈቃድ ሳያወጣ በጅምላም ሆነ በችርቻሮ ንግድ ላይ የተሳተፈ እንደሆነ ከብር 10ሺህ እስከ 100 ሺህ በሚደርስ የገንዘብ መቀጮ ይቀጣል ፤ የንግድ ድርጅቱም ይታሸጋል፡፡

• ማንኛውም ነጋዴ ስለሚሰጠው አገልግሎት ወይም ስለሚሸጠው እቃ የተሳሳተ መረጃ በማንኛውም ሁኔታ ለሸማቹ ከሰጠ ነጋዴው ለማግኘት ካቀደውና ካገኘው ትርፍ ጥቅም አንፃር ተሰልቶ ከብር 5ሺህ እስከ 10ሺህ በሚደርስ የገንዘብ መቀጮ ይቀጣል፡፡

• ማንኛውም ነጋዴ በፍጆታ እቃዎች ላይ ያለምንም በቂና ኢኮኖሚያዊ ምክንያት የዋጋ ጭማሬ በማድረግ ሽያጭ የፈፀመ እንደሆነ ከብር 10ሺህ እስከ 20ሺህ በሚደርስ የገንዘብ መቀጮ ይቀጣል፡፡

• ማንኛውም ነጋዴ በገበያ ላይ እጥረት ለመፍጠር በማሰብ መሰረታዊ የፍጆታ ዕቃዎችን ምርት የመደበቅና የማከማቸት ተግባር ላይ የተሳተፈ እንደሆነ ከብር 100ሺህ እስከ 200ሺህ ቅጣት ይጣልበታል።

• በሰው አካል ወይም ጤና ላይ ጉዳት ሊያደርሱ የሚችሉ እቃዎችን ከሌሎች ምግብ ነክ ከሆኑ ምርቶች ጋር በጋራ አድርጎ ማከማቸትና መሸጥ በሌሎች ህጎች በወንጀል የሚያስጠይቀው እንደተጠበቀ ሆኖ አስተዳደራዊ ቅጣት ከ100 ሺህ እስከ 300 ሺህ ብር ቅጣት ይጣልበታል፡፡

• ማንኛውም የንግድ ባዛር ከክልሉ ንግድና ገበያ ለልማት ፈቃድ ሳይሰጥ መስራት የተከለከለ ነው፡፡ ነጋዴው ከፈቃድ ሰጪ አካል ፍቃድ ሳይሰጠው በቀጥታ ወደ ስራ ገብቶ ከተገኘ ከብር 50ሺህ እስከ 100ሺህ የገንዘብ መቀጮ ይቀጣል፡፡ በተመሳሳይ ማንኛውም ባዛር አዘጋጅ የሆነ አካል ጥራታቸውን ያልጠበቁ እቃዎችን ለሽያጭ ካቀረበ ከብር 40ሺህ እስከ 60ሺህ በሚደርስ የገንዘብ መቀጮ ይቀጣል፡፡

• ማንኛውም በኮንትሮባንድ የነዳጅ ሽያጭ ግብይት ላይ የተሳተፈ አካል ከብር 300ሺህ እስከ 500ሺህ በሚደርስ የገንዘብ ቅጣት ተቀጥቶ የተያዘው ነዳጅ ይወረሳል፡፡

• ማንኛውም የቁም እንስሳ ነጋዴ በህገ ወጥ መንገድ ያለ ይለፍ ወይም ያለጉዞ መሸኛ የመጓጓ ፍቃድ ሳይኖረው የቁም እንስሳትን በመኪና ያጓጓዘ ወይም የቁም እንስሳትን ከግብይት ማዕከል፣ ከማደለቢያ ወይም ከእርባታ ቦታ ከተፈቀደው ርቀት በላይ በእግር የነዳ እንደሆነ ከብር 100ሺህ እስከ 200ሺህ በሚደርስ የገንዘብ መቀጮ ይቀጣል፡፡

• በሰንበት ገበያዎች ላይ የሚቀርቡ ምርቶችን መንግስት በሚያወጣው የዋጋ ተመንና የውል ስምምነት መሰረት ተግባራዊ የማያደርግ ማንኛውም ነጋዴ ከብር 5ሺህ እስከ 10ሺህ የገንዘብ መቀጮ ይቀጣል፡፡

• ማንኛውም በጥራጥሬ የኮንትሮባድ ምርቶች ግብይት ላይ የተሳተፈ አካል ከብር 200ሺህ እስከ 300ሺህ በሚደርስ የገንዘብ ቅጣት ተቀጥቶ የተያዘው የጥራጥሬ ምርት ይወረሳል፡፡